Content on this page requires a newer version of Adobe Flash Player.

Get Adobe Flash player

አርዕስት
‹‹የቀይ ሽብር›› ሰማዕታት ቤተሰቦችና ወዳጆች ማህበር የደርግ ባለሥልጣናት አቀረቡት በተባለው ‹‹የይቅርታና የእርቅ›› ጥያቄ በተመለከተ የጠቅላላ ጉባዔ የአቋም መግለጫ

የ‹‹ቀይ ሽብር›› ሰማዕታት ቤተሰቦችና ወዳጆች ማህበር ታህሳስ 24 ቀን 2003 ዓ.ም ባደረገው ጠቅላላ ጉባዔ በደርግ የሥልጣን ዘመን የተፈፀመ በደልና ጥፋትን በይቅርታና በእርቅ ለመጨረስ እንዲቻል በሚል የኢትዮጵያ የሃይማኖት መሪዎች የጋራ ሥራ ኮሚቴ በኩል  ለቀረበው የውይይት ጥሪ የማህበሩ ጠቅላላ ጉባዔ የሚከተለውን የአቋም መግለጫ አውጥቷል፡፡

‹‹የቀይ ሽብር›› ሰማዕታት ቤተሰቦችና ወዳጆች ማህበር የደርግ ባለሥልጣናት አቀረቡት በተባለው ‹‹የይቅርታና የእርቅ›› ጥያቄ በተመለከተ የጠቅላላ ጉባዔ የአቋም መግለጫ፡፡

በዘር ማጥፋት ወንጀል ተከሰውና ተፈርዶባቸው በእስር ላይ የሚገኙ የቀድሞ መንግሥት አባላት ‹‹የይቅርታና እርቅ›› ጥያቄ የኢትዮጵያ የሃይማኖት መሪዎች የጋራ ሥራ ኮሚቴ በኩል የ‹‹ቀይ ሽብር›› ቤተሰቦችና ወዳጆች ማህበር አባላትና አመራሩ በመስማቱ በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፊ ውይይት ለማካሄድና በጉዳዩ ላይ አቋም ለመያዝ ለአባላቱና ጉዳዩ ይመለከተኛል ለሚሉ ሁሉ በመገናኛ ብዙኃን ጥሪ ተላልፎ አባላቱና ለፍትሐዊ አሰራር ቆመናል የሚሉ ሁሉ ዛሬ ታህሳስ 24 ቀን 2003 ዓ.ም በ‹‹ቀይ ሽብር›› ሰማዕታት ቤተሰቦችና ወዳጆች ማህበር አዳራሽ ስብሰባ ተካሂዷል፡፡ በዚሁ ስብሰባ ላይ ደርግ ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ተወገደበት ጊዜ ድረስ በሥልጣን ላይ በነበረበት ወቅት የፈፀማቸው ኢፍትሐዊና ኢሰብዓዊ የነበሩ ድርጊቶች ሁሉ እጅግ መሪር በሆኑ ቃላት ከተሰብሳቢዎቹ በዝርዝር ቀርበዋል፡፡

ጉባዔው ከሰፊ ውይይት በኋላ ጉዳዩን በስፋት መርምሮና አጢኖ ከአንድ የጋራ አቋም ላይ ደርሷል፡፡

  1. የ‹‹ይቅርታና እርቁ›› ጥያቄ አቅራቢ ሆነው ባቀረቡት የሃይማኖት አባቶች በኩል ይህ የ‹‹ቀይ ሽብር›› ሰማዕታት ቤተሰቦችና ወዳጆች ማህበር እና ተጎጂ የሆነው እልፍ አዕላፍ ቤተሰቦች ፍጹም በማያውቁበት ሁኔታ ተቋቁሞ እንቅስቃሴና ቅስቀሳ በማድረግ ላይ መሆኑን የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡ በመሆኑም ተጠቂውና ተጎጂው እንዲሁም የከፍተኛ ስቃይ ሰለባ የሆነው አካል ሳያውቅ ይህንን መሰሉን ኮሚቴያዊ እንቅስቃሴ መደረጉን እንቃወማለን፡፡
  2. ከ1967 እስከ 1983 ዓ.ም ግንቦት ድረስ ከማንኛውም አገራዊም ሆነ ዓለም አቀፋዊ ሕግ ውጭ በሆነ ብሔራዊ ፋሺዝም የፖለቲካ ተቃዋሚዎች ናቸው በሚል መነሻ ብቻ ከ500000 በላይ ዜጎችን ያለአንዳች ፍርድ ሂደት በጅምላ እና በመሳሰሉት መንገዶች ከመጨፍጨፋቸውም በላይ በፖለቲካዊ መቻቻል ሊፈቱ የሚችሉ ሃገራዊ ጉዳዮችን በወታደራዊ አምባገነናዊ ጉልበት በመጠቀም ሕዝቦችን እርስ በእርስ በማፋጀት በሃገራች ሃገራዊ የፖለቲካ መዋቅር ላይ ከፍተኛ በደል የፈፀሙ በመሆናቸው ተጠየቀ የተባለው የይቅርታና የዕርቅ ጥያቄ ተቀባይነት የለውም፡፡
  3. ከላይ እጅግ ባጭሩ የተጠቀሰው አድራጎታቸው ሁሉ በፍርድ አደባባይ ሕግን መሰረት ባደረገ ሁኔታ ታይቶ በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግስት አንቀጽ 28 በሰብዕና ላይ ስለተፈጸሙ ወንጀሎች በሚለው አርዕስት ንዑስ አንቀጽ 1 እና 2 መሰረት ሕጋዊ ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡

በመሆኑም ከሕገ መንግሥቱ በላይ ሌላ ሕግ ባለመኖሩ በሕገ መንግሥቱ ላይ የተደነገገው የሕግ አንቀጽ በማንኛውም አካል ከኢትዮጵያ ሕዝብ ይሁንታ ውጭ ሊሻርም ሆነ ሊሻሻል ወይም ሊለወጥ ስለማይችል፡፡ ይኸው ሕግን መሰረት አድርጎ የተሰጠ ውሳኔ እንዲፀና መሆን አለበት የሚል አቋም አለን፡፡

  1. ተሰብሳቢዎቹ ከዚህ በላይ ያለውን ጉዳይ እጅግ በስፋት ከተወያየንበት በኋላ ‹‹የይቅርታና እርቅ›› ጥያቄውን በፍፁም እንደማንቀበል በሙሉ ድምፅ ከማረጋገጣችንም በላይ ወንጀለኞቹ ላደረሱት በደል ከእስራቱ ሌላ ሃገራዊና ዓለም ዓቀፋዊ ሕግ በሚፈቅደው መሰረት ተገቢውን ካሳ ለተጎጂዎች ሁሉ እንዲፈፅሙ በሕግ እንዲጠየቁ የጋራ አቋም ተወስዷል፡፡
  2. ይህ የጋራ አቋም መግለጫ በሃገሪቱ መገናኛ ብዙኃን እንዲሁም ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የሃገሪቱ መሪዎች ማለትም፡-

ሀ. ለኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት
ለ. ለኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር
ሐ. ለኢፌዲሪ ፌዴሬሽን ም/ቤት
መ. ለኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት
ሠ. ለኢፌዲሪ ፍትሕ ሚኒስቴር
ረ. ለኢፌዲሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
ሰ. ለዘጠኙ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስታትና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም  
ሸ. ለልዩ ልዩ የሃይማኖት ተቋማት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምፅ ወስነናል፡፡